Tag Archives: Ethiopian political parties

ከራሳችን ውጪ ለችግራችን ደራሽ መንግስት የለንም!

በወቅታዊ ጉዳዮች ላይ ከሰማያዊ ፓርቲ የተሰጠ መግለጫ

ከራሳችን ውጪ ለችግራችን ደራሽ መንግስት የለንም!

የኢትዮጵያውያን የውርደት ዘመን ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተባባሰ ሰሞኑን ከተከሰተው እጅግ አስከፊ ሁኔታ ላይ አድርሶናል፡፡ የመን ውስጥ በተከሰተው ጦርነት ተጎጂ የሆኑትን የውጭ ዜጎች መንግስታቶቻቸው ቀድመው ሲያስወጡ ለኢትዮጵያውያን ግን የሚደርስላቸው አልተገኘም፡፡ ይህንን ውርደትም ወገኖቻችን ‹‹የመን ውስጥ የቀረነው እኛና ውሻ ብቻ ነን፡፡›› ሲሉ እጅግ በሚያሳዝን መልኩ ገልጸውታል፡፡ ኢትዮጵያውያን ላይ የመድፍ፣ የሞርታርና የአውሮፕላን ድብደባ ሲዘንብባቸው በመከራ ላይ ያሉት ኢትዮጵያውያን ስልክ እንዲደውሉ በፌስ ቡክ ላይ በመለጠፍ ከማላገጥ ውጭ ምንም ያላደረገው የህዝብ ስልጣንን በሀይል የተቆጣጠርው ገዥው ፓርቲ ለራሱ ስልጣን ይጠቅሙኛል ያላቸውን የጦርነቱ ተሳታፊዎች ደግፎ መግለጫ ሲሰጥ የኢትዮጵያውያንን ስቃይ እጥፍ ድርብ አድርጎታል፡፡ በአጭሩ ኢህአዴግ ለራሱ ጥቅም ሲል ብቻ በማያገባውና በማይወጣው ዓለም አቀፍ ጦርነት ውስጥ ሀገራችንን ሲዘፍቅ ጦርነቱን ያወጀው የሚደርስላቸው ባጡ ምስኪን ኢትዮጵያውያንና በኢትዮጵያ ላይ ነው፡፡ ይህም የሀገራችን የውጭ ጉዳይ ፖሊሲ ከመቸውም ጊዜ በላይ የወደቀና ለዜጎች እንደማይቆም በድጋሚ ገሃድ የወጣበት ነው፡፡
በየመን የተከሰተውን መርዶ ሰምተን ሳንውል ሳናድር ደቡብ አፍሪካ ውስጥ በኢትዮጵያውያን ላይ ሌላ አስደንጋጭ አደጋና እና ሰቆቃ ልንሰማ ተገደናል፡፡ ኢትዮጵያውያን ሀብትና ንብረታቸው መዘረፉ ሳያንስ በአሰቃቂ ሁኔታ ህይወታቸው ሲያልፍ በዓለም አቀፍ ሚዲያዎች ተከታትለናል፡፡ የዚህ አሰቃቂ አደጋ ሰለባ የሆኑ የሌሎች ሀገራት ዜጎች በቶሎ ከደቡብ አፍሪካ ሲወጡ፣ እንዲሁም ሀገራቱ ዜጎቻቸውን መታደግ ያስችላል ያሉትን መፍትሄዎች ሲያስቀምጡ እና ሲያስጠነቅቁ ቢደመጥም ኢህአዴግ ግን እንደተለመደው የኢትዮጵያውያንን ሰቆቃና ስቃይ ከምንም እንዳልቆጠረው በግልፅ እየታየ ነው፡፡
በእርግጥ ላለፉት 24 ዓመታት ኢህአዴግ ሀገር ውስጥ የሚኖሩትን ዜጎች ሲያሰቃይ፣ በውጭ የሚኖሩትን ኢትዮጵያውያንም የሆነ ያልሆነ ስም እየለጠፈ በጠላትነት ሲፈርጃቸው እንደቆየ አይተናል፡፡ ከኢትዮጵያውያን ይልቅ የራሱን የግል ጥቅም ሲያሳድድም ቆይቷል፡፡ በቅርቡ ሳውዲ አረቢያ ውስጥ ወገኖቻችን ከፍተኛ በደል ሲደርስባቸው ይህ ነው የሚባል እገዛ ያላደረገው ኢህአዴግ ሰማያዊ ፓርቲ በወገኖቻችን ላይ የደረሰውን በደል በማውገዝ አዲስ አበባ ውስጥ የሚገኘው የሳውዲ ኤምባሲ ላይ ተገኝቶ ሲቃወም የሳውዲ ፖሊሶች ሀገራቸው ውስጥ ኢትዮጵያውያን ላይ ከፈፀሙት በደል ያልተናነሰ የኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ ሰልፍ በወጡት ኢትዮጵያውያን ላይ በጭካኔ ድብደባ ፈፅሟል፡፡ ይህም ኢህአዴግ ለኢትዮጵያውያን የቆመ ሳይሆን በበእድ አገራት በኢትዮጵያውያን ላይ በደል ከሚፈፅሙት ያልተናነሰ ጨካኝ ስርዓት መሆኑን ያሳየበት ነው፡፡ 
ኢህአዴግ ለስሙ ‹‹የዳያስፖራ ፎረም›› በሚል የራሱን ደጋፊዎች አደራጅቶ በውጭ የሚገኙ ኢትዮጵያውያንን ለልማት የበኩላቸውን እንዲያደርጉ እየሰራ እንደሚገኝ በስሩ በያዛቸው ሚዲያዎች ሲያሰራጭ ከርሟል፡፡ ከዚህም ባሻገር ኢትዮጵያውያኑ ለእነሱና ለሀገራቸው እንደማያስብ በመረዳታቸው ምክንያት ፊታቸውን ስላዞሩበት ውጤታማ አልሆነም እንጅ በተለያዩ አገራት እየተዘዋወረ ለአባይ ግድብ የበኩላቸውን እንዲያዋጡ ሲወተውት ታይቷል፡፡ ሳንቲም ለመልቀም በተለያዩ የዓለም ከተሞች እየዞረ ኢትዮጵያውያንን የሚሰበስበው ገዥው ፓርቲ በችግራቸው ወቅት ግን ምንም አይነት እርዳታ ሲያደርግ አይስተዋልም፡፡ ይብሱንም ችግር ላይ ባሉት ኢትዮጵያውያን ላይ ሌላ በደል ሲፈጽምና በስቃያቸው ላይ የማላገጥ ያህል ፕሮፖጋንዳ ሲሰራባቸው እያየን ነው፡፡ ይህም የሚያሳየው ገዥው ፓርቲ ኢትዮጵያውያንን አባብሎ ገንዘብ ከመቀበል ያለፈ ለውድ ህይወታቸው ደንታ እንደሌለው ነው፡፡
በኢትዮጵያውያን ላይ እየደረሱ ባሉት ተደጋጋሚ ግፎች ተሸፈነ እንጅ ሰሞኑን ሌላ ኢህአዴግ ለዜጎች እንደማይጨነቅ የታየበት ክስተት እየተፈፀመ እንደሆነ በተለያዩ ድህረ ገጾች ላይ ለመከታተል ችለናል፡፡ ኢህአዴግ ለራሱ ጥቅም ሲል ለሱዳን መንግስት አሳልፎ በሰጠው ሰፊና ለም የሀገራችን ሉዓላዊ መሬት አካባቢ የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን ላይ ሌላ አሳፋሪ እና አሰቃቂ ወንጀል እንደተፈፀመ ተዘግቧል፡፡ የሱዳን መንግስት ወታደሮች ድንበሩን ጥሰው የሱዳን አዋሳኝ በሆነው የሰሜን ጎንደር ዞን ጠረፋማ ቦታዎች የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን አርሶ አደሮች ላይ ጥቃት ሲፈፅሙ የኢትዮጵያ የመከላከያ ሰራዊት ሊታደጋቸው አልቻለም፡፡ 

ሰሞኑን በኢትዮጵያውያን ላይ የደረሰው ሰቆቃ ኢትዮጵያውያን አገራቸው ውስጥ ቢሆኑም ቢሰደዱም ከመከራው ሊላቀቁ እንዳልቻሉ አመላካች ነው፡፡ በውጭም ሆነ በሀገር ቤት የሚኖሩ የአንድ ሀገር ዜገች መብታቸውና ክብራቸው ሊጠበቅ የሚችለው ሀገር ውስጥ ለሀገርና ዜጎች የሚያስብና የሚቆረቆር መንግስት ሲኖር ነው፡፡ ሆኖም ኢትዮጵያውያን የሚገዙት ኢህአዴግን በመሰለ ለሀገርና ለህዝቡ ደንታ በሌለው ስርዓት በመሆኑ የሰሞኑ ሰቆቃ የሚገርም አይደለም፡፡ መቼውንም ኢህአዴግ የሀገርና የዜጎቹን መብትና ክብር ያስጠብቃል ብሎ መጠበቅም ዘበት ነው፡፡ 
ኢትዮጵያውያን የሀገራችንና የራሳችን ክብር እና ደህንነት ማስጠበቅ ካለብን መጀመሪያ ሀገራችን ላይ የሚገኘውን ስርዓት በፅኑ መታገል የግድ ይለናል፡፡ ኢትዮጵያ ውስጥ ምቹ አስተዳደር፣ ዴሞክራሲያዊና ለዜጎች የሚያስብ ስርዓት ቢኖር መጀመሪያውኑም ወገኖቻችን በገፍ ለአደጋ ወደሚጋለጡባቸው አካባቢዎች ባልተሰደዱ ነበር፡፡ በመሆኑም በቅድሚያ ክብራችንን ለማስመለስ የነፃነት ትግሉን አጠናክረን በመቀጠል፣ እንዲሁም በውጭ የምንገኝ ኢትዮጵያውያን ለጊዜውም ቢሆን ራሳችን ከአደጋ ለማዳን በተለያዩ ማህበራት ተደረጃቶ በመንቀሳቀስ ብሎም ስርዓቱ እስካለ ድረስ ችግሮቻችን እየተባባሱ እንጂ እየተቀረፉ እንደማይመጡ በመገንዘብ በሀገር ቤት ስርዓቱን ለመቀየር የሚደረገውን ሰላማዊ ትግል በማገዝ የችግራችንን ሁሉ መሰረት የሆነውን አምባገነናዊ አገዛዝ ለመለወጥ የበኩላችንን ልንወጣ ይገባል፡፡ ክብራችንን ልናስመልስ የምንችለው ሀገራችን ውስጥ እንዳንኖር ያደረገንን ስርዓት ቀይረን አንድም በገዛ አገራችን መኖር ስንችል፣ አንድም በአደጋ ወቅት ሊደርስልን የሚችል ተቆርቋሪና ለዜጎች የሚያስብ መንግስት መመስረት ስንችል ብቻ መሆኑን ልንገነዘበው ይገባል፡፡
በአሁኑ ሰዓት በደቡብ አፍሪካ ሰቆቃ እየደረሰባቸው ያሉ ወገኖቻችንን ለመታደግ በዓለም ላይ ተበትናችሁ የምትኖሩ ኢትዮጵያውያን በሙሉ በችግር ውስጥ ለወደቁት ወገኖቻችን አጋርነታችሁን በማሳየት ዓለማቀፍ የተቃውሞ ድምፃችሁን እንድታሰሙም ሰማያዊ ፓርቲ ጥሪውን ያስተላልፋል፡፡ በወገኖቻችን ላይ የሚደርሰውን ሰቆቃ እልባት እንዲያገኝ ፓርቲያችን የበኩሉን ጥረት እያደረገ ሲሆን በደቡብ አፍሪካ የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን ላይ የሚደርሰውን በደል ለማስቆም አዲስ አበባ በሚገኘው የደቡብ አፍሪካ ኤምባሲ በኩል የራሱን ጥረት እያደረገ ይገኛል፡፡ በሌላ በኩል የመን ውስጥና በሱዳን አዋሳኝ የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን ላይ ስርዓቱ ከባዕዳን ጋር ተባብሮ የሚፈፅመውን በደልም ለህዝብና ለዓለም አቀፍ ማህበረሰቡ በማጋለጥ የበኩሉን አስተዋጽኦ ለማድረግ መረጃዎችን እያሰባሰበ ይገኛል፡፡

በትግላችን የሀገራችንና የራሳችን ክብርና መብት እናስጠብቅ!

ኢትዮጵያ በክብር ለዘላለም ትኑር!!!

ሚያዝያ 9/2007 ዓ.ም

image

image

image

የአውሮፓ ህብረት 10 ተቃዋሚ ፓርቲዎችን በምርጫው ጉዳይ አነጋገረ

በነገረ ኢትዮጵያ

image

• ጠቅላይ ሚኒስትሩንም ምሽቱን ያነጋግራል ተብሎ ይጠበቃል

• ህብረቱ ምርጫውን አይታዘብም ተብሏል

የአውሮፓ ህብረት ልዑክ ዛሬ ህዳር 11/2007 ዓ.ም ሶስት የተቃዋሚ ፓርቲዎች መሪዎችን ያነጋገረ ሲሆን፣ በኢህአዴግ በኩል ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርያም ደሳለኝን ለማነጋገር ምሽቱን ቀጠሮ መያዙን ለማወቅ ተችሏል፡፡ 

በአውሮፓ ህብረት የልዑል መሪ ሻንታል ሔቤሬት የተመራው የልዑካን ቡድን የሰማያዊ ፓርቲና የ9ኙ ፓርቲዎች ትብብር ሊቀመንበር ኢንጅነር ይልቃል ጌትነትን፣ እንዲሁም የመኢአድና የመድረክን አመራሮች ማነጋገራቸው ታውቋል፡፡

የአውሮፓ ህብረት ሶስቱን ተቃዋሚ ፓርቲዎች ያነጋገረበት ዋነኛው አላማ ከምርጫ 2007 በፊት ያሉትን ችግሮች ለማወቅ የሚል ሲሆን በተቃዋሚዎቹ በኩል ያሉትን ችግሮች ለጠቅላይ ሚኒስትሩ እንደሚያቀርቡ ገልፀዋል፡፡ 

የሰማያዊና የ9ኙ ፓርቲዎች ትብብር ሊቀመንበር ኢ/ር ይልቃል የአውሮፓ ህብረት ላቀረበው ጥያቄ በርካታ ችግሮች መኖራቸውን በማመልከት፣ ‹‹የምርጫው ችግር ከአጠቃላይ የኢትዮጵያ ችግር የመነጨ ነው፡፡ በተለይ ከ1997 ዓ.ም በኋላ ሚዲያውን፣ ሲቪክ ተቋማቱንና ተቃዋሚዎችን ለማፈን መሳሪያ የሆኑ አዋጆች የአገሪቱን ፖለቲካ አበላሽተዋል፡፡ በምርጫው ላይ የተፈጠረው ችግር የዚህ ሁሉ ድምር ነው›› በማለት መሰረታዊ የአገሪቱ ችግሮች ካልተፈቱ ምርጫው ላይ የተደቀነው ችግርም ሊፈታ እንደማይችል እንደገለጹላቸው ለነገረ ኢትዮጵያ ገልጸዋል፡፡

በሌላ በኩል ከአሁን ቀደም የተደረጉትን ምርጫዎች የታዘበውና በምርጫዎች ሂደት ነበሩ የተባሉትን ችግሮች በሪፖርቱ በማካተት የሚታወቀው የአውሮፓ ህብረት ስለ ምርጫው ሁኔታ በቅርቡ ስላወቀና ቀድሞ ስላልተጋበዘ ምርጫውን እንደማይታዘብ የተቃወቀ ሲሆን በአንጻሩ የአፍሪካ ህብረት ምርጫውን እንደሚታዘብ ከወዲሁ ለመረዳት ተችሏል፡፡

የ9ኙ ፓርቲዎች ትብብር ለኃይማኖት ተቋማት ጥሪ አቀረበ

Semayawi Party- Ethiopia

image

ጥቅምት 12 ቀን 2007 ዓ.ም 9 ተቃዋሚ ፓርቲዎች የመሰረቱት ትብብር ‹‹ነጻነት ለፍትሃዊ ምርጫ›› በሚል ለአንድ ወር የሚቆይ የመጀመሪያ ዙር የህዝባዊ ትግል ፕሮግራሙን ጥቅምት 25/2007 ዓ.ም በሰማያዊ ፓርቲ ጽ/ቤት ይፋ ማድረጉ ይታወቃል፡፡

የ9ኙ ፓርቲዎች ትብብር በአንድ ወር መርሃ ግብር ተግባራዊ ከሚያደርጋቸው መካከል የመጀመሪያው በቤተ እምነት ጸሎት እንዲደረግና ጥሪ ማቅረብና አማኞች እንደየ እምነታቸው ተሳትፎ እንዲያደርጉ ማድረግ ሲሆን ይህን ጥሪም ዛሬ ህዳር 1/2007 ዓ.ም ለኃይማኖት ተቋማት አቅርቧል፡፡

(ነገረ ኢትዮጵያ የጥሪውን ሙሉ ክፍል ለአንባቢዎቿ እንደሚከተለው አቅርባዋለች፡፡)

ከ9ኙ ፓርቲዎች ትብብር የተላለፈ አገራዊ የጸሎት ጥሪ

በኢትዮጵያ የተቃዋሚ ፖለቲካ ፓርቲዎች ትብብር

አገራችን የክርስትናና እስልምና ኃይማኖቶችን በመቀበል ቀደምት በመሆኗ ብቻ ሳይሆን የኃይማኖቶቹ ተቋማት፣አባቶችና ምዕመናን በመከባበርና መቻቻል አብረው በሠላም በመኖር ለዓለም ህዝብ ተምሳሌት መሆናችን የምንኮራበት ነው፡፡ ለዚህም የቤተ እምነቶቹ አባቶች ለምዕመናኑ ያስተማሩት የሞራልና ሥነ-ምግባር እሴቶችና በአብሮነት ላይ የቆመ የአገር ፍቅር ስሜት፣ እነዚህንም እንዲጠብቋቸውና እንዲያከብሯቸው አርዓያ በመሆን ያደረጉት አስተዋጽኦ ከፍተኛ ነው፡፡

አገራችንና ህዝቧ በተፈጥሮ ሚዛን መዛባት በሚከሰትም ሆነ በአገዛዝ ሥርዓቶች ምክንያት በችግር ውስጥ በሚወድቁበት ጊዜ ሁሉ የእነዚህ ኃይማኖቶች ተቋማትና ምዕመናን መዓቱ እንዲርቅና ምህረቱ እንዲወርድ ፈጣሪያቸውን በጾምና በጸሎት በመለመን/ በመማጸን፣ በሃይማኖታዊ የሞራልና ሥነ ምግባር እሴቶቻቸው መሠረት በመተዛዘን ፣ በመረዳዳትና በመተጋገዝ የተገኘውን በመካፈል በአብሮነት ስሜት በርካታ ክፉ ጊዜያትን መሻገራቸው በታሪክ ተመዝግቦ ይገኛል፡፡

ዛሬ ላይ እነዚህ የሞራልና ሥነ-ምግባር እሴቶች እየተናዱ በመሄዳቸው ዜጎች ለማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ ምስቅልቅል ተጋልጠዋል፣ የአገር ፍቅር ስሜት በጥያቄ ውስጥ ወድቋል፡፡ በዚህም በመቻቻል ፋንታ ግጭትና መፈናቀል በአራቱም አቅጣጫ ህዝብን ለሥቃይና ሥጋት ዳርጓል፣ የህግ ‹‹አምላክ›› ክብር እያጣ ፍትህ እየተዛባ ነው፣ ወህኒ ቤቶች በታሳሪዎች ተጨናንቀዋል፣ የምግብ ተረጂውና የጎዳና ላይ ተዳዳሪው ዜጋ ቁጥር ተበራክቷል፣… በአጠቃላይ የህዝባችን ኑሮና ህይወት፣ የአገራችን ሠላምና መረጋጋት ፈታኝና አሳሳቢ ደረጃ ላይ ናቸው፤ የዜጎች ተስፋ በመናመኑ የህይወት ዋጋ በሚጠይቅ ሁኔታ ውስጥ እየተሰደዱ በባዕድ አገር ለአደጋ እየተጋለጡ ነው፡፡

በሌላ በኩል ደግሞ በአገራችን ያሉ የተፎካካሪ ፓርቲዎች/ገዢው ፓርቲና ተቃዋሚዎች/ ተጨባጩን ሁኔታ የሚመለከቱበትና የሚረዱበት መንገድ በሁለት ጫፍ ላይ በመወጠሩ የጋራ መፍትሄ ለማምጣት ያለው ዕድል በአስቸጋሪ ሁኔታ ውስጥ በመሆኑ ችግሮቹን እያባባሰ ይገኛል፡፡ ስለዚህ፡-
በአገራችን ውስጥ በተለያየ ምክንያት በሁለት ጠርዝ ላይ የቆሙ ኃይሎች ወደ ብሄራዊ መግባባትና ዕርቅ እንዲመጡ፣ በህዝብ ውስጥ የሚታየው የሞራልና ሥነምግባር ጉድለት እንዲቃናና የመቻቻልና መተሳሰብ ስሜት እንዲያንሰራራ፣ የዜጎች ሥቃይና ሥጋት ተወግዶ በተስፋ እንዲሞላ፣….፤

በአገራችን መረጋጋትና ዘላቂ ሠላም እንዲሰፍን፣ ቀጣይና ዘላቂ ልማት እውን እንዲሆን፣ አብሮነታችንና አንድነታችን እንዲጠናከር፣ የአገር ፍቅር ስሜት እንዲለመልምና ለሉዓላዊነታችን ያለን ቀናዒነት እንዲጠናከር፣….፤

በሰንበትና የጁምኣ ቀናት በጋራ እንዲሁም በየግል የዘወትር ጸሎት ፈጣሪ አምላክን በመለመን ለተያያዝነው አገራዊ ዓላማና የጋራ ጥረት ድጋፋችሁን እንድታደርጉ ለየቤተ እምነት ኃላፊዎች /ቤተ ክርስቲያናትና መስጂዶች/ እና ለምዕመናን በሙሉ ጥሪያችንን እናቀርባለን፡፡

ፈጣሪ አምላክ አገራችንንና ህዝቧን ከጥፋት ይታደግ ዘንድ በጸሎት እንትጋ!!

ኅዳር 01 ቀን በ2007 ዓ.ም፣ አዲስ አበባ

ከ9ኙ ፓርቲዎች ትብብር የተሰጠ መግለጫ

የ9ኙ ፓርቲዎች ትብብር የመጀመሪያ ዙር ህዝባዊ ትግል ፕሮግራሙን ይፋ አደረገ

• የ24 ሰዓት (የአዳር) የተቃውሞ ሰልፍ ተጠርቷል

በነገረ ኢትዮጵያ ሪፖርተር

ጥቅምት 12 ቀን 2007 ዓ.ም 9 ተቃዋሚ ፓርቲዎች የመሰረቱት ትብብር ‹‹ነጻነት ለፍትሃዊ ምርጫ›› በሚል ለአንድ ወር የሚቆይ የመጀመሪያ ዙር የህዝባዊ ትግል ፕሮግራሙን ዛሬ ጥቅምት 25/2007 ዓ.ም በሰማያዊ ፓርቲ ጽ/ቤት ይፋ አደረገ፡፡

‹‹ነጻነት በሌለበት ፍትሃዊ ምርጫ የማይታሰብ በመሆኑ የተዘጋውን በር ለመክፈት የ‹ነጻነት ለፍትሃዊ ምርጫ› በሚል የፕሮግራም መርሃ ግብር ለመክፈት ወስኖ የመጀመሪያው ዙር እንቅስቃሴ በአዲስ አበባ ከተማ ለማድረግ›› እንዳዘጋጀ ያሳወቀው ትብብሩ የትግሉ ዓላማ ፍትሃዊ ምርጫ እንዲኖር የሚያስችል መሆኑን ገልጾአል፡፡

‹‹ምርጫ ቦርድ ለገዥው ፓርቲ ያለውን ወገናዊነትና ጉዳይ አስፈጻሚነት ፍንትው አድርጎ አሳይቷል›› ያለው መግለጫው በመጀመሪያ ዙር የአንድ ወር ፕሮግራሙ 6 ዋና ዋና ተግባራትን ለመፈጸም ዝርዝር እቅዶችን አውጥቶ ዝግጅቱን ማጠናቀቁን አስታውቋል፡፡ በህዳር ወር የሚያከናውናቸው ተግባራትም፡-

1. በቤተ እምነት ጸሎት እንዲደረግና ጥሪ ማቅረብና አማኞች እንደየ እምነታቸው ተሳትፎ እንዲያደርጉ ማድረግ
2. የአደባባይ ህዝባዊ ስብሰባዎችን ማድረግ
3. የተቃውሞ ድምጽ ማሰማት (ሰላማዊ ሰልፍ)
4. ለመንግስት ተቋማት ደብዳቤ ማስገባት
5. በምርጫ ዙሪያ የፓናል ውይይቶችን ማድረግና
6. የህዝብን ተሳትፎ ማበረታታትና ድጋፍ ማሰባሰብ እንደሆኑ በመግለጫው አሳውቋል፡፡

ከእቅዶቹ መካከልም በሶስት ተከታታይ እሁዶች በተለያዩ የአዲስ አበባ ክፍሎች 3 የአደባባይ ስብሰባዎች እንደሚኖሩ፣ በመጨረሻው መርሃ ግብርም ህዳር 27ና 28 በፕሮግራሙ ማጠቃለያነት የ24 ሰዓት (የውሎና የአዳር) የተቃውሞ ሰልፍ እንደሚደረግ የትብብሩ ሊቀመንበር ኢንጅነር ይልቃል ጌትነት ገልጸዋል፡፡

በገዥው ፓርቲና በምርጫ ቦርድ ጥምረት ይፈጸማል ያለውን ህገ ወጥ ተግባር በመታገል ለሰላማዊ ትግሉ አወንታዊ አስተዋጽኦ ለማበርከት እስከመጨረሻው በፅናት ለመቆም መዘጋጀቱን የገለጸው ትብብሩ በአገር ቤትና በውጭ የሚገኙ ኢትዮጵያውያን፣ በትብብሩ ሂደት ቆይተው እስካሁን ያልፈረሙና ሌሎች ፓርቲዎች እና የዓለም አቀፉ የዲፕሎማቲክ ማህበረሰብ ከጎኑ እንዲቆሙ ጥሪ አቅርቧል፡፡

image

image

image

image

Eprdf charged senior opposition party members from BlueParty, Arena and UDJ with terrorism & attempt to illegally overthrow the government

እነ የሽዋስን ጨምሮ 10 ተጠርጣሪዎች በይፋ ክስ ተመሰረተባቸው

• አብርሃ ደስታ የሁለት ድርጅቶች አባል ነው የሚል ክስ ተመስርቶበታል

• ወደ አዲስ አበባ ማረሚያ ቤት እንዲዘዋወሩ ታዟል

በነገረ ኢትዮጵያ ሪፖርተር

image

በልደታ የፌደራሉ ከፍተኛ ፍርድ ቤት አራተኛ ምድብ ወንጀል ችሎት ዛሬ ጥቅምት 21/2007 ዓ.ም ከቀኑ ዘጠኝ ሰዓት አካባቢ በተሰየመው ችሎት 10 ተከሳሾች በፌደራል አቃቢ ህግ በይፋ ክስ ተመሰረተባቸው፡፡ ተጠርጣሪዎቹ ከ100 ገጽ በላይ የክስ ቻርጅ የተነበበላቸው ሲሆን ከክስ ቻርጁ ጋር ከ300 ገጽ በላይ የምርመራ ሰነድ ቀርቦባቸዋል፡፡

የክሱ መዝገብ የተከፈተው ዘላለም ወርቃገኘሁ በተባለውና ‹‹የግንቦት 7 አመራር ነው፡፡›› ተብሎ ክስ በተመሰረተበት ግለሰብ ሲሆን በዚህ የክስ መዝገብ የተካተቱትም፡-

1ኛ ተከሳሽ ዘላለም ወርቃገኘሁ
2ኛ ተከሳሽ ሀብታሙ አያሌው
3ኛ ተከሳሽ ዳንኤል ሺበሺ
4ኛ ተከሳሽ አብርሃ ደስታ
5ኛ ተከሳሽ የሽዋስ አሰፋ
6ኛ ተከሳሽ ዮናታን ወልዴ
7ኛ ተከሳሽ አብርሃም ሰለሞን
8ኛ ተከሳሽ ሰለሞን ግርማ
9ኛ ተከሳሽ ብርሃኑ ደጉ
10ኛ ተከሳሽ ተስፋዬ ተፈሪ ናቸው

ለሁሉም ተከሳሾች ከዛሬ በፊት ክስ እንዳልደረሳቸውና ዛሬ ፍርድ ቤት ውስጥ እንደተሰጣቸው ታውቋል፡፡ በችሎቱ 6ኛ ተከሳሽ ከሆነው ዮናታን ወልዴ በስተቀር ሁሉም ያለ ጠበቃ የቀረቡ ሲሆን ጠበቃዎቹ ያልቀረቡበት ምክንያትም ጠበቆቹ ደምበኞቻቸው የሚቀርቡበት ቦታና ጊዜ ስላልተነገራቸው እንዲሁም ቀደም ብለው እንዳይገናኙ በመደረጋቸው መሆኑን አቶ ኃብታሙ አያሌው ችሎቱ ላይ ተናግሯል፡፡

ከሳሹ የፌደራል አቃቢ ህግ በ1996 የወጣው የወንጀል ህግ እና የጸረ ሽብር ህግ ጠቅሶ ክስ ያቀረበ ሲሆን ክሶቹ በሁለት ዋና ዋና ጭብጦች ቀርበዋል፡፡ የመጀመሪያው ጭብጥ ‹‹ከሽብርተኛ ቡድኖች ጋር በጋራ በመስራት›› የሚል ሲሆን ‹‹ህገ መንግስቱንና ህገ መንግስታዊ ስርዓቱን በኃይል ለመናድ፣ የመንግስትን መሰረተ ልማት በማፈራረስ፣ ህዝብን ለአመጸ በማነሳሳት መንግስትን መለወጥ አላማው አድርጎ ከሚሰራውና ራሱን ግንቦት 7 ብሎ ከሚጠራው ቡድን ጋር አባል በመሆንና በወንጀል ድርጊቶች በመሳተፍ›› በሚል ቀርቧል፡፡

ሁለተኛው የክስ ጭብጥ ‹‹የሽብር ቡድን አመራር በመሆን›› የሚል ሲሆን በተለይም የአንደኛ ተከሳሽ ዘላለም ወርቃገኘሁ ‹‹የሽብር ቡድኑ አመራር በመሆንና አባል በመመልመል›› በሚል የክስ ጭብጥ ቀርቦበታልል፡፡

ከ2-5ኛ የክስ መዝገብ የሚገኙት ማለትም ሀብታሙ አያሌው፣ ዳንኤል ሺበሽ፣ አብርሃ ደስታና የሸዋስ አሰፋ ‹‹ህጋዊ የፖለቲካ ፓርቲን ከለላ በማድረግ ግንቦት 7 የተባለውን የሽብር ቡድን አላማ ለማሳካት ተንቀሳቅሰዋል፡፡ ፋሲል የኔ ዓለምና ሌሎች የሽብር ቡድኑ አባላት ጋር በስልክ በመነጋገርና በማህበራዊ ድህረ ገጸ የተለያዩ መልዕክቶችን ተለዋውጠዋል›› የሚል ክስ ቀርቦባቸዋል፡፡ አብርሃ ደስታ ከግንቦት 7 በተጨማሪ ‹‹ደምኢት የተባለ ቡድን አባል ነው፡፡›› የሚል ክስ ቀርቦበታል፡፡

በስተመጨረሻም ፍርድ ቤቱ ሁለት ጉዳዮች ላይ ውሳኔ ሰጥቷል፡፡ አንደኛው ረቡዕ ጥቅምት 26/2007 ዓ.ም 3 ሰዓት ተከሳሾቹ ዋስትና ይሰጣቸው አይሰጣቸው በሚለው ጉዳይ ላይ ፍርድ ቤቱ ከተከሳሾቹ ጠበቆች ጋር ተማክሮ ውሳኔ ይሰጣል ተብሏል፡፡ በሁለተኛነት ተጠርጣሪዎቹ ባቀረቡት አቤቱታ መሰረት ቀደም ሲል ለአራት ወራት ወደቆዩበት ማዕከላዊ እስር ቤት እንዳይመለሱ ፍርድ ቤቱን ስለጠየቁ ፍርድ ቤቱ በአዲስ አበባ ማረሚያ ቤት (3ኛ) እንዲቆዩ ትዕዛዝ ሰጥቷል፡፡

ተከሳሾቹ ትናንት ጥቅምት 20/2007 ዓ.ም አራዳ ምድብ ችሎት ይቀርባሉ ተብሎ የነበር ቢሆንም ሳይቀርቡ ቀርተዋል፡፡ በተመሳሳይ ዛሬ ጥቅምት 21/2007 ዓ.ም ጠዋት ወደ ልደታ ፍርድ ቤት ተወስደው የነበረ ቢሆንም እንደገና ወደማዕከላዊ ተመልሰው ከሰዓት እንዲቀርቡ ተደርገዋል፡፡

ከሰማያዊ ፓርቲ በወቅታዊ ጉዳዮች ላይ የተሰጠ መግለጫ

ነገረ ኢትዮጵያ / Negere Ethiopia
ከሰማያዊ ፓርቲ 

በወቅታዊ ጉዳዮች ላይ የተሰጠ መግለጫ

ሰማያዊ ፓርቲ ከተመሰረተበት ጊዜ አንስቶ በሕብረተሰቡ ዘንድ የሚነሱ በርካታ መሰረታዊና ወቅታዊ ጥያቄዎችን ጥያቄዎቹ አድርጎ ሲንቀሳቀስ መቆየቱ ይታወቃል፡፡ ባለፉት ሁለት አመታት ውስጥም ፓርቲያችን በተለያየ መልኩ የተቻለውን ሁሉ በማድረግ እየታገለ በመንግስት ላይ ጫና ለማሳደርና ችግሮች መፍትሔ የሚያገኙበት አቅጣጫ ሲያመለክት ቆይቷል፡፡ ይሁን እንጂ የሀገራችን አስተዳደራዊና ፖለቲካዊ ችግሮች ከግዜ ወደ ግዜ እየተባባሱና እየከፉ የመምጣታቸውን ያህል ገዢው ፓርቲ ቆም ብሎ ከማሰብ ይልቅ ወደ ማይወጣው አዘቅት ውስጥ ሀገሪቷን ጭምር እያንደረደራት ይገኛል፡፡ ይህም አልበቃ ብሎ ከዲሞክራሲያዊ ስርዓት ግንባታ ሂደት ፍፁም በማይጣጣም መለኩ ዜጎችን ለአንድ ሀሳብ ብቻ እንዲገዙ አስገዳጅ መንገዶችን ጭምር በመጠቀም አፋኛ መዋቅሩን በማናለብኝነት እያስፋፋ ይገኛል፡፡ ይህም አልበቃ ብሎ ለማናቸውም አስተዳደራዊም ይሁን ፖለቲካዊ ጥያቄዎች ሀይልን በመጠቀም ለመደፍጠጥና ለማጥፋት ቆርጦ በመነሳት ፍፁም አምባገነንነቱን ገፍቶበት የበርካቶች ህይወት ተቀጥፏል፡፡

ለዚሁ እንደማሳያም:-

ካለፈው ዓመት የክረምት ወራት መጨረሻ አንስቶ እስከ አሁን ድረስ ዜጎች በተለያየ ዘርፍ በመከፋፈል የግዳጅ ስልጠና እየሰጠ ይገኛል፡፡ በዚህ አስገዳጅ ስልጠናም የምርጫ ቅስቀሳ በሚመስል መልኩ ከህወሓት/ኢህአዴግ ውጪ አማራጭ እንደሌለ ከመስበክ ባለፈም ማናቸውም የተለየ ሀሳብ የሚያራምዱ የህብረተሰብ ክፍሎችን፣ ድርጅቶችንና ግለሰቦችን ፍፁም ስነ ምግባር በጎደለው መልኩ የጥላቻ ዘመቻ በማካሄድ የሃሳብ ልዩነትን የማስተናገድ ፍላጎቱ ሙሉ ለሙሉ የተዳፈነ መሆኑን አሳይቷል፡፡ ለዚህ ህገወጥ እንቅስቃሴ እና ዓላማም ወደ 1 ቢሊየን የሚጠጋ የህዝብ ሃብት ባክኗል፤ እየባከነም ይገኛል፡፡ ሰማያዊ ፓርቲ እነዚህን ስልጠናዎች እጅግ በቅርበት ሲከታተላቸው የቆየ ሲሆን ከጅማሬውም ተቃውሞውን በይፋ ማሰማቱ ይታወሳል፡፡ 

በሌላ በኩል የሕብረተሰብ የመረጃ ክፍተት ለመሙላት እና ካለበት የፖለቲካ ድብርት ለማውጣትና ለማነቃቃት ሕገ መንግስቱን መሰረት አድርገው ሃሳባቸውን በነፃነት የገለፁ ጋዜጠኞችና የህትመት ውጤቶቻቸው ከገበያ እንዲወጡ በማተሚያ ቤቶች በኩል አስተዳደራዊ ሴራ መስራቱ ሳያንስ ሕገ መንግስቱን በሚፃረር መልኩ በሕትመት ሚዲያዎቹ ባለቤቶች፣ አዘጋጆች፣ በጋዜጠኞቹና ሰራተኞቻቸው ላይ በማስፈራራት ስነ ልቦናዊ ጫና በማሳደር በርካቶች ለስደት ሲዳረጉ ጥቂቶች ደግሞ ለእስር ተዳርገዋል፡፡ ገዢው ፓርቲ ባንድ በኩል ሀሳቡን ለመጫን የግዳጅ ስልጠና እየሰጠ በሌላ በኩል ደግሞ የተለየ ሀሳብን እንዲሁም የህዝብ ብሶትን የሚያሰሙ ጋዜጠኞች ላይ የማሳደድ ዘመቻ መክፈቱ የስርዓቱን መበስበስ እና አፋኝ አምባገነንነትን ብቸኛ አማራጭ አድርጎ መቀጠል መምረጡን ግልጽ አመላካች ነው፡፡

ከላይ ከሰፈሩት ሁነቶች እጅግ የከፋውና እየተባባሰ የመጣው ሌላው ከፍተኛ አደጋ ያዘለ ችግር ደግሞ፤ አስተዳደራዊ እና ፖለቲካዊ ጥያቄ እያነሱ ያሉ የሕብረተሰብ ክፍሎችን በሀይል ለመገዛት ቆርጦ መነሳቱ ነው፡፡ ባሳለፍናቸው ሁለት ወራት ብቻ ቁጥራቸው ቀላል የማይባል ዜጎች በመንግስት ሀይሎች ተገድለዋል – ቆስለዋል – ተሰደዋል፡፡ በኦጋዴን መንግስትን የተቃወሙ ዜጎች ወደ ግጭት እንዲገቡ በሚገፋፋ መልኩ ጥያቄዎቻቸውን በመግፋት በርካታ ዜጎች በመንግስት ሀይሎች ህይወታቸው መቀጠፉ ሳያንስ ሬሳቸው እንኳን ክብር በሌለው ሁኔታ መሬት ለመሬት እየተጓተተ ባደባባይ ሰብአዊ መብት ሙሉ ለሙሉ ተጥሷል፡፡ በጋምቤላም በተመሰሳይ መልኩ የህወሓት ሰዎች መሬት በሕገ-ወጥ መንገድ መቀራመታቸውን የተቃወሙ ዜጎች ወደ ግጭት የተገፉበት እና በርካታ የሰው ህይወት የተቀጠፈበት ሁነት እጅግ አሳዛኝ እና መንግስት የተያያዘው መንገድ ወደ ከፋ ሁኔታ ሀገሪቷን እየወሰዳት ለመሆኑ ማረጋገጫ ነው፡፡

ሰማያዊ ፓርቲ ከላይ የተዘረዘሩትንና ከዚህ ያልተጠቀሱትን በተለያየ የሀገሪቱ ክፍሎች የሚፈፀሙትን በርካታ የሰብዓዊ መብት ጥሰቶች እና አስጊ ሁኔታዎች በቅርብ እየተከታተለ ይገኛል፡፡ በተደጋጋሚ እንደተገለፀውም አሁን ካለንበት ሀገራዊ አዘቅት እና አደጋ መውጫው መፍትሔ በቆራጥነት ሀገርን የማዳን ትግል ማካሄድ እንደሆነ ፓርቲያችን በሚገባ ይገነዘባል – ያምናል፡፡ በስልጠናዎቹ ወቅትም ተማሪዎች እና በርካታ የሕብረተሰብ ክፍሎች በብዛት ሲያነሱት የነበረውን ጥያቄና ስሞታም ከግንዛቤ በማሰገባት ጥያቄዎቹ ምላሽ የሚያገኙበትን የትግል አቅጣጫ በተጠናከረና በተጠና መልኩ አሳታፊ አድርጎ ከግብ ለማድረስ በሙሉ ቁርጠኝነት እና አቋም ላይ እንደሚገኝ ያረጋግጣል፡፡

በመሆኑም የሀገሪቱን ወቅታዊ ሁኔታ ከግምት በማሰስገባት መላው የሀገሪቱ ህዝብ፣ በውጪ የምትኖሩ ኢትዮጵያዊያን እና ለሀገር ተቆርቋሪ ተቋማት እንዲሁም በገዢው ፓርቲ ኢህአዴግ ስር ሆናችሁ ለውጥን የምትሹ ወገኖች ሀገራችንን ወደ አደጋ እየወሰዳት ያለውን አፋኝ ስርዓት በቻላችሁት ሁሉ በመቃወምና ከስርዓቱ ጋር ባለመተባበር በብሔራዊ ደረጃ የሚደረገው ትግል አካል እንድትሆኑ ጥሪውን ያስተላልፋል፡፡ 

ኢትዮጵያ በክብር ለዘላለም ትኑር!

ጥቅምት 18 2007 ዓ.ም

ሰማያዊ ፓርቲ 

አዲስ አበባ

image

image